የሻው ስንሻው
ኢትዮጵያ አገራችን በሩቁም ሆነ በቅርብ ዘመን ታሪኳ ወታደሮቿ በሙያ ብቃት እና በወታደራዊ ሥነ-ምግባር አብዝተው የሚታሙ አልነበሩም፡፡ በግዳጅ አፈጻጸም፤ በንጹኃን ሰዎች መብት ጥበቃ እና በምርኮኛ አያያዝም ጭምር የሠራዊቱ ስም እንዲህ እንደ ዛሬው የጎደፈበት ዘመን ያለ አይመስለኝም፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት እና መሪዎቹ ለአገሬው ዜጋ ይቅርና ለወራሪው የአውሮፓ ቅኝ ገዥ የጦር ምርኮኞች እንዴት ያለ ቸርነት እንዳደረጉ ጠላት ሳይቀር የማያብለው ሐቅ ነው፡፡ የጠላትን ጦር ቁስለኞች በማከም፤ የተራቡትን በማብላት፤ የተጠሙትን በማጠጣት፤ የጦር ምርኮኞች አያያዝ ምስጉን ስም ያተረፈ ሠራዊት ነበረን፡፡ ለዚህ ደግሞ ቱርኮችም፤ ጣሊያኖችም፤ ግብጾችም እማኞች ናቸው፡፡ ሶማሌያውያን እና ሱዳኖችም ቢሆኑ ይህንን እውነት አይክዱትም፡፡
ሠራዊታችን የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ ተልዕኮ ተቀብሎ የተሰማራው በአሜሪካ ሠራሹ እና በምዕራብ መራሹ ኮሪያን ለሁለት በከፈለው ጦርነት መሆኑ ይታወሳል፡፡ በኮሪያ ልሣነ ምድር የቃኘው ሻለቃ አባላት የፈጸሙት ጀብድ እና ያስመዘገቡት ገድል ዛሬም በደቡብ ኮሪያ እና በኢትዮጵያ መካከል የመገናኛ ድልድይ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ በውጊያ ቆይታው ጥቂት ቆስለውበት፤ በጣት የሚቆጠሩ ጀግኖች ወድቀው፤ አንድም ወታደር ያላስማረከው የቃኘው ሻለቃ አባላት ስም ዝርዝር በወርቅ ቀለም ታትሞ በሁለቱ አገራት መታሰቢያ ቆሞላቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሠራዊት በተባበሩት መንግሥታት ጥላ ስር በኮንጎ ኪንሻሳ የሁለት ዙር የሠላም ማስከበር ስምሪት አድርጓል፡፡ የላይቤሪያን የእርስ በእርስ ጦርነት እልባት በማስገኘት ረገድ የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ሠራዊት ሚና ከፍ ብሎ ይወሳል፡፡ በሩዋንዳ የነበረው የዘር ፍጅት በዚያ አስከፊነቱ እንዳይቀጥል በማድረጉ ጥረት አገራችን አሰማርታው በነበረ የሠላም ማስከበር ሠራዊት አክብሮት ተችራለች፡፡ በሶማሊያ፤ በሱዳን ዳርፉር እና አቢዬ ግዛቶች ስምሪት የወሰደው ሠራዊትም ቢሆን በአገሩ የውስጥ ፖለቲካ የተነሳ ልቡ ይሻክር እንጂ ተልዕኮውን በአግባቡ መወጣትን አስመልክቶ ስምሪቱን ከሰጠው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ይሁን ከየአገራቱ ዜጎች የቀረበበት ይህ ነው የሚሰኝ የሥነ-ምግባር ጉድለት የሚያጣቅስ የክስ ዶሴ አልነበረም፡፡
አሁን ያለው መለዮ ለባሽ ግን በፍጹም ከአገር መከላከያ ሠራዊት መርህ በአፈነገጠ መልኩ ሕጻናትን ጨምሮ ሴቶችን ይደፍራል፡፡ ከተቃራኒ ወገን የሆነ ቁስለኛን ከሆስፒታል አልጋ ላይ ወስዶ ይገድላል፡፡ ጥበቃ ሊያደርግላቸው የተገባ ያልታጠቁ ንጹኃን ዜጎችን በአደባባይ ይረሽናል፡፡ በቤተ እምነቶች እና በትምህርት ተቋማት ውስጥ መሽጎ ይተኩሳል፡፡ አገርን እና ሕዝብን ከዘራፊ የመከላከል ተልዕኮውን ወደ ጎን ትቶ ራሱ በአስጸያፊ የዘረፋ ተግባር ስለመሰማራቱ ዜጎች በምሬት ይገልጻሉ፡፡ የአገርን ዳር ድንበር እና የግዛት አንድነት የማስጠበቅ ቃለ መሐላውን ዘንግቶት ሲያበቃ ደመወዝ እየከፈለ በሚያስተዳድረው ምስኪን አርሶ አደር ላይ ፍጅት ይፈጽማል፡፡ ጦሩ በጠላትነት የፈረጀው ወገን ለምሣሌ ፋኖ “ውረድ እንውረድ” ብሎ ወዲያ ከመስኩ እየጠበቀው ሳለ እርሱ ግን መሃል ከተማን የሙጥኝ ብሎ በሠላማዊ ዜጎች መኖሪያ ቤት፤ ንብረት እና ተቋማት ላይ ቦምብ እና አዳፍኔ ያዘንባል፤ መድፍ እና መትረየስ ያዥጎደጉዳል፡፡ ሕዝቡ ለጠላት መመከቻ ገዝቶ ያስታጠቀውን መሣሪያ ለወገን ፍጅት ያውለዋል፡፡
የመከሊከያ ሠራዊት አዋጅ ቁጥር 1100/2011፤ አንቀጽ 9 “የሠራዊት አባላት ግዴታ” በሚል ርዕስ ስር ማንኛውም የሠራዊት አባል:- (1). “የአገሪቱን ሉዓላዊነት እና ዳር ድንበር የመጠበቅና የመከላከል ግዴታ አለበት”፤ … (6) “ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅት ወገናዊነት ነፃ በሆነ አኳኋን የማከናወን ግዴታ አለበት” ሲል ይደነግጋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን በምናስተውለው መሬት ላይ በሚታየው እውነታ ከላይ የተቀመጡት ግዴታዎች በማያሻማ መልኩ በአፍራሻው እየተተገበሩ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ እስኪ እነዚህን ሁለት ግዴታዎች ጥቂት በጥቂቱ ዳሰስ እናድርጋቸው፡፡
የአገሪቱን ሉዓላዊነት እና ዳር ድንበር የመጠበቅና የመከላከል ግዴታ
ዛሬ ኢትዮጵያ በተለያየ አቅጣጫ ድንበሯ ተጥሶ እና ሉዓላዊነቷ ተደፍሮ ይገኛል፡፡ ከአልጀርሱ ስምምነት ጋር በተያያዘ እያወዛገበ የዘለቀውን እና የፖለቲካ ውሳኔ የሚጠይቀውን የባድመን ጉዳይ ለጊዜው እናቆየው፡፡ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የሱዳን ጦር እስከ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቆ፤ ኢትዮጵያውያንን ገድሎ፤ ዘርፎ እና አፈናቅሎ የአልፋሽጋን አካበቢ ከወረረ ሦስት ዓመት ሊደፍን ቀናት ይቀሩታል፡፡ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያን አንድ ወረዳ አስለቅቃ የራሷን የአስተዳደር እና የጸጥታ መዋቅር ተክላ ከኢትዮጵያ ምድር የወርቅ ማዕድን በማውጣት ላይ ትገኛለች፡፡ ቀደም ሲል በትግራይ አሁን ደግሞ በአማራ ክልሎች በመካሄድ ላይ የሚገኙት ጦርነቶች የልብ ልብ የሰጡት የአፍሪካ ቀንድ ነውጠኛ አልሻባብ በሱማሊያ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሠራዊት ከመተናኮልም አልፎ ወደ አገራችን ድንበር ዘልቆ ጥቃት በመሰንዘር ላይ ይገኛል፡፡ ነገ በቦረና እና በቱርካና ሐይቅ በኩል ምን ሊፈጠር እንደሚችል አለመጠርጠርም ቢሆን ጂኦ ፖለቲካዊ ተላላነት ይመስለኛል፡፡
በኢትዮጵያ ሕዝብ አንጡራ ኃብት የሚተዳደረው እና በጎሰኞች የሚዘወረው መከላከያ ሠራዊት ግን የአገሩን ሉዓላዊነት ካለማስደፈር እና ዳር ድንበሯን ከማስከበር ይልቅ የገዛ ራሱን ዜጎች በመፍጀት ሥራ ላይ ተጠምዷል፡፡ የእርስ በእርስ ጦርነት አሸናፊ እና ተሸናፊ የለውም፡፡ በሁለቱም ወገን የሚወድቁት የአንድ አገር ልጆች ከመሆናቸው የተነሳ ለዕለት ጥቅም የወንድምን ደም ማፍሰስ የሕሊና እረፍት የለውም፡፡ በመጨረሻም በለስ በቀናው እና ዕድል ፊቷን ባዞረችበት ወገን መካከል የሚካሄድ የበቀል መቆራቆዝ ይከተላል፡፡ ጠነን ያለ እንደሆነም “የእገሌ ሠራዊት” ተብሎ የዜግነትን መብት ጭምር በመግፈፍ ለጉስቁልና፤ ለረኃብ እና እርዛት አሳልፎ መሰጠትም ይመጣል፡፡ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት የአገር ኪሣራ ይሆናል፡፡ በታሪክ አጋጣሚ አገዛዝ በተፈራረቀ ቁጥር ገዥዎች የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ይልቅ የዙፋናቸው ዘብ አድርገው የሚያዋቅሩት ሠራዊት የኋላ ኋላ ለአገሩም ለራሱም የማይጠቅም ከንቱ ይሆናል፡፡ አገዛዝ ያልፋል፤ አገርና ሕዝብ ግን ይቀጥላል፡፡
ስለዚህ አሁን በሕዝብ ላይ ቃታ በመሳብ ላይ የምትገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ሆይ፤ ቅጥር ስትፈጽሙ በቃለ መሐላ የተቀበላችሁት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ዳር ድንበር የመጠበቅና የመከላከል አደራ አደጋ ላይ መውደቁን ተገንዝባችሁ ሳይረፍድ በጊዜ የምትገኙበትን ሁኔታ መርምሩ፡፡ ሕዝብን ተዋግቶ የሚያንበረክክ ገዥም ሆነ የሚያሸንፍ ሠራዊት አለመኖሩንም አትዘንጉ፡፡ ይልቁኑ እናንተም አገራችሁን እንዳታጡ፤ አገርም እናንተን እንዳታጣ በሚያስችል መልኩ አቋማችሁን ፈትሹ፡፡
የመከላከያ ሠራዊቱ ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅት ወገናዊነት ነፃ በሆነ መልኩ ማከናወን
ሠራዊቱ በቃለ መሐላ ከተቀበላቸው ግዴታዎች ሌላኛው እንዲህ ይነበባል “ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅት ወገናዊነት ነፃ በሆነ አኳኋን ማከናወን”፡፡ አሁን እየሆነ የሚገኘው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ በሥራ ስምሪቱም ሆነ በግዳጅ አፈጻጸሙ ሠራዊት አዛዡን ይመስላል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ዛሬ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ከላይ ሆነው የሚያሰማሩት ሰዎች የዘውግ ፖለቲካ አቀንቃኝ ካድሬዎች ናቸው፡፡ የሚሳሳቡት፤ የሚሿሿሙት እና የሚወዳደሱትም ጭምር እዚያው በዚያው ነው፡፡ ሸማኔዎቹ “ድር በድር” እንዲሉ፡፡ በዚህ ረገድ ገሐዱን እውነታ በጥቂቱ ጨረፍ ላድርግላችሁ፡፡
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዡ ትውልዳቸው ከሁለት ወገን መሆኑን ቢያስነግሩም የዘውግ ፖለቲካ ገና በለጋ ዕደድሜያቸው ተጣብቶና ተጠናውቷቸው ትምህርታቸውን ከሰባተኛ ክፍል አቋርጠው በኦሕዴድ የተጠመቁ “የበዳይ ተበዳይ” ትርክት ሰለባ ናቸው፡፡ አስገራሚ አቋራጮችን ተጠቅመው (የትምህርታቸውን ደረጃ እና የወታደራዊ ማዕረጋቸውን ጉዳይ የማንሳት ፍላጎት የለኝም) የሥልጣኑን መንበር ከተቆናጠጡ በኋላም ቢሆን ያንኑ ያዲያቆናቸውን ከፋፋይ ፖለቲካ ከማራመድ የተለየ አቅጣጫ አልተከተሉም፡፡ የበዓለ ሲመታቸው ሰሞን አሳይተውት የነበረው የአንድ ገቢር ትወና የብዙዎቻችንን አድናቆት ቢያጎርፍላቸውም የሁሉም ኢትዮጵያዊ መሪ የመሆን ካርዳቸውን በገዛ እጃቸው አቃጥለዉ በጎጥ ጉያ ገብተው ተወሸቁ፡፡ አሁን አሁን የካርዱ ቃጠሎ ጥቀርሻው ይሰነፍጣቸው ይዟል፡፡
ሌላው ሠራዊቱን የማሰማራት ኃላፊነት የተጣለባቸው፤ አዋጅ ሳይወጣ ጭምር የልዑል ራስነት ማዕረግ የተቸራቸው ኤታማዦር ሹሙ ያለፉበት እና ያገደሙበት መንገድ የጎጥ ፖለቲካ አቀንቃኝነታቸውን አይሸሽግላቸውም፡፡ ኤታማዦር ሹሙን ለየት የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር ወታደራዊ ጉዟቸውን በኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ዓላማ ስር ጀምረው የከፋፋይ አገዛዝ ዋና ገጸ-ባሕርይ ሆነው ብቅ ማለታቸው ይሆናል፡፡ ከገንጣይ አስገንጣዮች ጋር ይፋለም የነበረው ሠራዊት አባል ሆነው አገልግለዋል (ከአየር ወለድ ምድብተኝነት ወደ እግረኛ ተዋጊነት የተዛወሩበትን የቅጣት ምስጢር ራሳቸው ቢያወጉን ይሻላል)፡፡ ኋላ ላይ በምርኮ ከዚያኔ ጠላቶቻቸው እጅ ላይ ወደቁ፡፡ ቀጥሎም በኤርትራ እና ትግራይ ምድር በአንድነት ጎራ ሆነው ከተፋለሟቸው ቡድኖች ጋር ተወዳጅተው በሌላ መለዮ ብቅ አሉ፡፡ ያኔ ማርከው ይገለገሉባቸው የነበሩት አለቆቻቸው ቀን ዘንበል ሲልባቸው ደግሞ እነሆ ከአምስት ዓመታት ወዲህ ሦስተኛውን መለዮ አጥልቀው ተከስተዋል፡፡ በዚህ የማይጨበጥ እና የማይገመት ተለዋዋጭ ግለ ሰብዕናቸው የተነሳ ጦሩን የት ቅርቃር ውስጥ ወስደው እንደሚዶሉት ሳይታለም የተፈታ ይሆናል፡፡ ስለ ኤታማዦር ሹሙ አራተኛ መለዮ ለመተንበይ አሰብኩና …
አየር ኃይሉን፤ ምድር ጦሩን፤ የልዩ ዘመቻ ሠራዊቱን፤ ኮማንዶ እና አየር ወለዱን፤ ፌደራል ፖሊሱን ወዘተርፈ እነማን እያሰማሩት እና አገሪቱን ወዴት እየወሰዷት እንደሆነ ቆም ብሎ ለመመርመር ቢዘገይም አልረፈደም፡፡ እነዚህ ሰዎች በደኃ ሕዝብ ልጆች እልቂት የሥልጣን ዘመናቸውን ማራዘም የሚፈልጉ፤ አገርን እያደኸዩ እነርሱ በምዝበራ ኃብት በማካበት ሥራ የተጠመዱ፤ የኢትዮጵያ አንድነት እና ሉዓላዊነት ግድ የማይሰጣቸው ናቸው፡፡
ሲጠቃለል፤ አሁን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እየተመራ የሚገኘው በዘውግ ፖለቲካ በተጠመቁ እና በፍቅረ ንዋይ በናወዙ ሰዎች መሆኑን በውል ተገንዝቦ ጦሩ ራሱን ከሕግ ተጠያቂነት እና ከታሪክ ተወቃሽነት እንዲያርቅ መጠየቅ አማራጭ የሌለው የወቅቱ ጥሪ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የአገር ፍቅር፤ ለሕዝብ ክብር እና ወታደራዊ ዲሲፕሊን የሌለው የጦር አዘዥ ሠራዊቱንም ራሱንም ይዞ ይጠፋል፡፡ ዳፋውና ዕዳው ግን የአገርና የሕዝብ ይሆናል፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተሳተፉ የጀርመን ወታደሮች ለጀርመን ሕገ-መንግሥት ሳይሆን ለመሪያቸው ለአዶልፍ ሒትለር ታማኝነታቸውን በቃለ-መሐላ እንዲያረጋግጡ ተደርጎ ነበር፡፡ የናዚን ሽንፈት ተከትሎ ወታደሮቹ በሰብዓዊ ፍጡር (በተለይም በአይሑዶች) ላይ ታይቶ እና ተሰምቶ የማያውቅ መከራ በማዝነባቸው በኑረምበርግ ችሎት ፊት ቀርበው ፍርዳቸውን ሲከናነቡ ለአምባገነኑ መሪያቸው የገቡት ቃለ-መሐላ እንደ ቅጣት ማቅለያ እንኳን አልተቆጠረላቸውም፡፡