በአማራ ክልል በደብረ ታቦር ከተማ በመከላከያ ሰራዊት እና የፋኖ ህዝባዊ ታጋዮች መካከል ከሁለት ቀናት በላይ በዘለቀው ውጊያ በቅርቡ የተሾመት የፋርጣ ወረዳ አዛዥ ኮማንዶር አዲሱ መገደላቸው ተገለፀ ።
የኢቪኤን ምንጮች እንደገለጹት ፋኖዎች በፖሊስ የመሳሪያ ግምጃ ቤት የነበረውን መሳሪያና ጥይት ለመውስድ በሞከሩበት ወቅት በተነሳ አለመግባባት በተከፈተው ተኩስ ልውውጥ ኮማንደር አዲሱ ላይ እርምጃ መወሰዱ ታውቋል።
በጦርነቱ በርካታ የመከላከያ ወታደሮች ቁስለኛ ሆነው ወደ ደብረ ታቦር ሆስፒታል መወሰዳቸው ተገልጿል። መከላከያው ከእብናት ኃይል ጨምሮ በመምጣቱ የፋኖ ተዋጊዎች አፈግፍገው ከከተማው እንደወጡ ከእማኞቹ ለመረዳት ተችሏል። ካለፈው ቅዳሜ እስከ ሰኞ አምስት ሰዓት ድረስ ከባድ ጦርነት እንደተካሄደና የከተማው ነዋሪዎችና ሁለት የፋኖ አባላት መገደላቸውን ኢቪኤን ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልፀዋል።
ከተማው ወደ ሙሉ እንቅስቃሴ ባለመመለሱ የደረሰውን ሙሉ ጉዳት ለማወቅ አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል፡ ከቀኑ 12 ሰዓት በኋላ ሰዓት እላፊ እንደተጣለና ባጃጆች ምንም አይነት የትራንስፖርት አገልግሎት እንዳይሰጡ መከልከሉ ተሰምቷል።
የመከላከያ ወታደሮች ቤት ለቤት እየፈተሹ የፋኖ አባላትን ለማደን እየሞከሩ መሆኑን ምንጮቹ ገልፀዋል።